Sunday, September 13, 2015

ከብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት እና ከፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብር ሀይል የተሰጠ መግለጫ::ከብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት እና ከፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብር ሀይል የተሰጠ መግለጫ ለበርካታ አመታት በኤርትራ መንግስት አማካይነት ሲደራጅ የነበረ የጥፋት ሀይል ብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት በዚህ ሀይል ውስጥ ከነበሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ምስጢራዊ የሆነ የግንኙነት ስርዓት በመመስረት በተሰራው የተቀናጀ የኦፐሬሽን ስራ አማካይነት በተደራጀ መልኩ ከነሙሉ ትጥቁና የሰው ሀይሉ ጋር መስከረም 1 ቀን 2008 . . ወደ ሃገሩ እንደገባ የጋራ ፀረ ሽብር ሀይሉ አስታውቋል፡፡ የኤርትራ መንግስት ባደራጀው የጥፋት ሀይል ውስጥ ከሚገኙ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር የተጀመረው ግንኙነት ከአንድ አመት በላይ የቆየ እድሜ ያስቆጠረ ሲሆን በአንድ በኩል ሃገራችን በማስመዝገብ ላይ ያለችው ፈጣን ልማትና እድገት የፈጠረባቸው ተፅእኖ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የሃገራችንን ልማትና ሰላም ለማደናቀፍ የቆረጡ የኤርትራ መንግስትና የሌሎች ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች የጥፋት አጀንዳ እየተረዱ የመጡና በምንም መንገድ የዚህ የጥፋት ተልእኮ መሳርያ በመሆን ማገልገል የለብንም የሚል ጠንካራ እምነት የያዙ የቡድኑ የአመራር አባላት ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት በመመስረት በተለያየ መንገድ የኤርትራ መንግስትንና የሌሎች አሸባሪ ሀይሎችን የጥፋት ተልእኮ በማኮላሽት በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚሁም መሰረት በቅርቡ የኤርትራ መንግስትና ግንቦት 7 የተባለው አሸባሪ ፀረ ኢትዮጵያ ድርጅት ባዘጋጁት የህብረት ስምምነት ላይ የስብስቡ ኮር ሀይል የሆነው ዴምህት የተባለው ድርጅት ሊቀመንበርና በሻዕቢያና በግንቦት 7 የተመሰረተው ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን የተመረጠው ሞላ አስገዶም ከመንግስት በተሰጠው ተልእኮ መሰረት ሌሎች ሃገር ወዳድ ጓደኞቹን በማሳመንና በማደራጀት የሻዕቢያን የጥፋት ተልእኮ ሲያከሽፉና አጠቃላይ ሂደቱን መንግስት በሚፈልገው መንገድ ሲመሩት ከቆዩ በኋላ ግዳጃቸውን እጅግ አኩሪ በሆነ መንገድ ፈፅመው ሀይላቸውን እንዳለ ከነሙሉ ትጥቁ በመያዝ ወደ እናት ሃገራቸው ተመልሰዋል፡፡ አቶ ሞላ አስገዶምና ሌሎች ሃገር ወዳድ ጓደኞቹ ምንም እንኳን ስለሃገራችን ጥፋትና ውድመት ሌት ተቀን የሚያልመው የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን የማጥፋት ፍላጎት በሚገባ ከተረዱ በኋላ ቶሎ ብለው ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በዚህ ከአንድ አመት በላይ የዘለቀ ምስጢራዊ ግንኙነት ከብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት የሻዕቢያንና የሌሎች የጥፋት ሀይሎችን ተንኮልና ሴራ እያከሸፉ እንዲቆዩና መጨረሻ ላይ መንግስት በሚወስነው ጊዜና ወቅት ላይ ግዳጃቸውን በሚፈለገው መንገድ አጠናቅቀው እንዲወጡ በተደረሰው መግባባት መሰረት ኦፐሬሽኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ ለረጅም ጊዜ እየተመራ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜም አቶ ሞላና ሌሎች ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውን ጓደኞቹ በኤርትራ መንግስት የሚሰጣቸውን የጥፋት ግዳጅ እንዲመክን በማድረግ፣ ኢንፎርሜሽኑ አስቀድሞ ለብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በማቀበል አስፈላጊ የሆነ ጥንቃቄ እንዲደረግ በማገዝ፣ 2 ኤርትራ ውስጥ የሚካሄደውን ፀረኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በተመለከተ ወቅታዊ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ወቅታዊ መረጃ እንዲደርስ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ከመጫወታቸውም በላይ ኤርትራ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ተቃዋሚ የሚባሉ ድርጅቶች ዘንድ የአሸባሪው የግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆነው ብርሃኑ ነጋ አሜሪካ ውስጥ ተቀምጦ አርበኞች ከሚባለው ድርጅት ጋር የተፈፀመውን ውህደት በሊቀመንበርነት ትግሉን መምራት የለበትም የሚል የጋራ አቋም እንዲይዙ በማድረግ ብርሃኑ ነጋ ሳይወድ ተገዶ ወደ አስመራ እንዲገባ ማድረግ ችለዋል፡፡ አሸባሪው ብርሃኑ ነጋ በተፈጠረበት ጫና ተገዶ ኤርትራ ከገባ በኋላ እዛው ከሚገኙ የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች ጋር ውህደት ለመፍጠር የነበረው ከፍተኛ ፍላጎትና ግፊት ሞላ አስገዶምና እሱ የሚመራው ድርጅት ተቀብለው እንዲገቡ ከተስማሙ በኋላ ፀረ ኢትዮጵያ ሴራውን ለማኮላሸት በማግስቱ ሀይላቸውን ይዘው ኤርትራን ለቀው እንዲወጡ በተደረሰው መግባባት መሰረት ውህደቱ ተከናወነ ተብሎ በኤርትራ መንግስትና በተላላኪዎቹ ብዙ ዳንኪራ ከተደለቀበት በኋላ ሞላ አስገዶምና ሃገር ወዳድ ጓደኞቹ አስቀድሞ የተሰጣቸውን ግዳጅ በመፈፀም ወሽመጣቸው እንዲቆረጥ አድርገዋል፡፡ በሞላ አስገዶምና በጓደኞቹ የሚመራው 800 በላይ የሚሆን በሚገባ የታጠቀና የተደራጀ ሀይል አስቀድሞ በጋራ በተዘጋጀው እቅድ መሰረት በሁመራ በኩል ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ወደ ሃገራቸው ጉዞ ከጀመሩ በኋላ በአንድ የሻዕቢያ ቅጥረኛ ከሃዲ አማካይነት በመጨረሻ ሰዓት ላይ ምስጢሩ ለሻዕቢያ ጆሮ በመድረሱና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የነበረው ግንኙነት በድንገት የተቋረጠ ቢሆንም በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ፈጣን የሆነ እርምጃ በመውሰድ እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት ባለቀ ሰዓት መረጃው ከደረሰው በኋላ በድንበር አከባቢ የነበረ ሀይሉን በፍጥነት ወደ ኡምሃጀር በማንቀሳቀስ መንገድ ዘግቶ ለማቆም ሙከራ ያደረገ ቢሆንም በሞላ አስገዶም የሚመራው ሀይል ኦምሃጀርና ቀጥሎም ሱቅ አልከቲር በሚባል የድንበር ኬላ ላይ የጠበቀውን የኤርትራ መንግስት ሰራዊት ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ እና በጠላት እጅ ሊወድቅ ይችላል ብሎ የገመተውን ንብረትና ተሽከርካሪ በማቃጠል ወደ ሱዳን ሀምዳይት ተሻግሯል፡፡ በጉዞ ላይ እንዳሉ በገጠማቸው የጠላት ሀይል ምክንያት በሁለት ግንባር በኩል በተካሄደው ውጊያ በሞላ አስገዶም የሚመራው አመራር መንገድ በመዝጋት በቅድሚያ 400 በላይ የሚገመት ሀይል እንዲሻገር ካደረገ በኋላ ቀጥሎም ሞላ አስገዶም እና አብዛኛው የቡድኑ አመራር የነበረበት ከኋላ የነበረው 300 በላይ የሚሆን ሀይል ወደ ሃምዳይት መሻገር ችሏል፡፡ በዚህ ውጊያ ከኤርትራ መንግስት በኩል በርካታ ወታደሮች የተደመሰሱ ሲሆን በሞላ አስገዶም ከሚመራው ሀይልም ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቁ ታጣቂዎች የመሞትና የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ በሌላ ግንባር የነበሩ ቁጥራቸው ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የሞላ አስገዶም ሀይሎች የኤርትራ መንግስት ሰራዊትን ትኩረት ለማዛባት በሶስተኛ ግንባር በኩል በከፈቱት ውጊያ ራሳቸውን ከጠላት ጥቃት እየተከላከሉ በቀጥታ ከኤርትራ ተነስተው ወደ ሁመራ መግባት ችለዋል፡፡ በየቦታው ተንጠባጥቦ የነበረ ሀይል አሁንም ወደ ሱዳንና ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ የቀሩት እና መውጣት ያልቻሉ የቡድኑ አባላት በሽተኞች፣ 3 በየቦታው የነበሩ እስረኞች፣ የኪነት ቡድን አባላትና ሌሎች አቅመ ደካሞች ብቻ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህ ኦፐሬሽን በድል እንዲጠናቀቅ ከጅምሩ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ሲሆን የአማራ ክልላዊ መንግስትና የመከለከያ ሀይላችንም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምን ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ልማት የቅርብ አጋር የሆነው የሱዳን መንግስትም እነዚህን ታጣቂዎች ሱዳን መሬት ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ከኤርትራ መንግስት ወታደሮች ጥቃት በመከላከል፣ አስፈላጊውን ምግብና መጠለያ በማቅረብ፣ በውጊያው ለቆሰሉ የቡድኑ ታጣቂዎች ተገቢውን የህክምና እርዳታ በመስጠት እና በመጨረሻም ሀይሉን ከነሙሉ ትጥቁና ድርጅቱ በተሽከርካሪ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ በማጓጓዝ በሰላም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ላደረገው ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ አስተዋፅኦ በኢትዮጵያ መንግስት ስም የጋራ የፀረ-ሽብር ግብረ ሃይሉ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ መስከረም 2/2008


0 comments:

Post a Comment