Saturday, April 25, 2015

መንግስት የሚጠበቅበትን ኣስቸኳይ እርምጃዎች ይውሰድ!

ያሳለፍነው ሳምንት መላው ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጡና የተቀረውን የኣለም ህዝብ ጭምር ያሳዘኑ ክስተቶችን ኣስተናግዶ ኣልፏል። በደቡብ ኣፍሪካ የሚኖሩ ኣፍሪካውያን ስደተኞች ላይ ኣገሬዎቹ ባደረሱት ጥቃት ከሶስት የማያንሱ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። የተረፉትም ከዛሬ ነገ ተገደልን በሚል በሰቆቃ ላይ ይገኛሉ። ይሄን ክስተት በተለየ ኣስደንጋጭ የሚያደርገው ኣገሬዎቹ ስደተኞቹን ለማስወገድ የተከተሉት መንገድ ነው። እንደግሪሳ እየተመሙ ያገኙትን ዜጋ ያልሆነ ኣፍሪካዊ ዘግናኝ በሆነ መልኩ በድንጋይ በመደብደብ፣ በስለት ደጋግሞ በመውጋትና በእሳት በማቃጠል ጣእረ ሞቱን በማራዘም ነው የሚገድሉት። ደቡብ ኣፍሪካውያን መጀመሪያ ከቅኝ ግዛት ከዚያም በኋላ ከኣፓርታይድ ኣገዛዝ እንዲወጡ ከፍተኛ ኣስተዋጽኦ ያደረጉት መላ ኣፍሪካውያን በተለይም ደግሞ ታላቁ መሪያቸውን ኔልሰን ማንዴላን ከማሰልጠን ጀምሮ፣ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ትግል በሊግ ኦፍ ኔሽንስና በተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ላይ ያደረግነው ኢትዮጵያውያን ቁጭታችን የከፋ ሆኗል።

በዚህ ክስተት ተደናግጠን ሳናበቃ በሰሜን ኣፍሪካዊቷ ሊቢያ ደግሞ ይበልጥ ኣስደንጋጭ የሆነ ክስተት ሰማን።  ራሱን እስላማዊ መንግስት ወይም ደግሞ ዳዕሽ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ሃያ ስምንት ኢትዮጵያውያንና ሁለት ኤርትራውያንን በኣሰቃቂ ሁኔታ ኣንገታቸውን በመቅላትና በጥይት ኣናታቸውን በመበርቀስ ገድሏቸዋል። በዚሁ ሳምንት ከስምንት መቶ የማያንሱ ስደተኞችን የጫነች መርከብ ሰጥማ ቁጥራቸው ያልታወቀ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከሌሎች ኣፍሪካውያን ስደተኞች ጋር ኣብረው ሞተዋል። እነኚህ ሶስት ክስተቶች ቀድሞውንም በሳውዲ ኣርቢያ፣ በኩዌት፣ በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በየመን፣ በሱዳን፣  በደቡብ ሱዳን፣ እና በሌሎችም ኣገራት የተሰደዱ ኢትዮዽያውያን በሚደርስባቸው ግፍና መከራ ኣንጀቱ ሲቆስል የቆየውን መላ ኢትዮጵያዊ ከብሄር ብሄር፣ ከሃይማኖት ሃይማኖት ሳይለይ ባንድነት በቁጣ አንዲገነፍል ኣድርጎታል።
ይህን ተከትሎም በእለተ ማክሰኞ ሚያዚያ 13 2007 ዓ.ም. የሁለት ሟቾች ቤተሰቦችና የኣዲስኣበባ ነዋሪዎች የሁለቱን ሟቾች ፎቶግራፎች በመያዝ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሲሆን፣ መንግሥት የጠራው ሠልፍ ስላለ ተብሎ በፖሊስ ተበትኗል፡፡  በማግስቱም መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ መላው ህዝብ የተሳተፈ ሲሆን በዚሁ ሰልፍ ላይ የሃይማኖት መሪዎችና ባለስልጣናት ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራውን ቡድንና በኢትዮጵያውያኑ ላይ የፈጸመውን ድርጊት ኣውግዘዋል።
ታዲያ በዚህ ሰልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናትቀድሞም የጀመርነውን ፀረሽብር ዘመቻ ኣጠናክረን እንቀጥላለን” ከማለት በስተቀር ኣሁን በደቡብ ኣፍሪካም ሆነ በሊቢያ የሚገኙ ዜጎችን ከሚደርስባቸው ግፍና መከራ ለመታደግ ስለሚደረግ እርምጃ ሲናገሩ ኣልተደመጠም። መንግስት ሲጀምርም ባሳየው ዳተኝነት የተበሳጩት ቀጥሎም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ኣይነት ተጨባጭ መፍትሔ ያልሰሙት በሰልፉ ተገኝተው የነበሩ ወጣቶች ብስጭታቸውን በመፈክርና በጩኸት ለማሰማት ሞክረዋል። ፖሊስም ሁኔታውን ለማረጋጋት ሲሞክር በተፈጠረ ግጭት ሰልፉ ሲበተን ዜጎችም ለጉዳትና ለእስር ተዳርገዋል። በተመሳሳይ መልኩ መንግስት ኣንገብጋቢ የሆነውን በሊቢያና በደቡብ ኣፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ችግር ለመፍታት ዜጎችን ወደ ኣገራቸው ለመመለስ ከተደረገ የታይታ ጥረት ባሻገር ኣስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነት ኣለማሳየቱ በኣገር ውስጥም ሆነ ከኣገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ኣስቆጥቷል።
በርግጥ በስደት የሚኖሩ ዜጎቻችን ያለባቸው ችግር የተወሳሰበና ብዙ የረጅም ጊዜ ዘለቄታዊ መፍትሔዎች የሚያስፈልጉት ነው። የስደትን ችግር ከምንጩ ማድረቅንና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ኣያያዝን ዘለቄታዊ መፍትሔዎች በተመለከተ በሌላ ፅሁፍ የምመለስበት ሲሆን ለዛሬ  መንግስት በኣስቸኳይ ሊወስዳቸው የሚገባ ኣንዳንድ  እርምጃዎችን ለመጠቆም እሞክራለሁ።  እነኚህም ስራዎች የመልሶ ማቋቋም ስራዎች፣ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችና፣ ወታደራዊና የደህንነት ስራዎች ናቸው።
መንግስት በሊቢያ፣ በየመንና በደቡብ ኣፍሪካ የሚኖሩ ወደኣገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ኢትዮዽያውያን ለመመለስ ኣስቸኳይ ግብረሃይል ሊያቋቁም ይገባዋል። ይህ ግብረሃይል በየኣገራቱ ከሚገኙ ቆንስላዎችና ኤምባሲዎች ጋር በመቀናጀት ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ለማጣራት በየኣገራቱ ካሉ የተለያዩ መንግስታዊኣካላትና መንግስታዊ ያልሆኑ ኣካላት ጋር በመተባበር ዜጎች ያሉባቸውን ቦታዎች፣ ብዛታቸውን፣ የደህንነት ሁኔታቸውን እና ሌሎች መረጃዎች ማጥናትና ኣጠቃላይ ሪፖርት ማቅረብ በዚያም መሰረት ኣስቸኳይ ተግባራዊ እን ቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል።  በዚህም መሰረት መመለስ የሚፈልጉትን ኢትዮጵያውያን ባስቸኳይ ወዳገራቸው መመለስና ከተመለሱም በኋላ መልሰው የሚቋቋሙበትን ፕሮግራም ቀርጾ ማስፈጸም ያስፈልጋል።
ሌላው በኣስቸኳይ ሊደረግ የሚገባው ኣፋጣኝ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን መውሰድ ነው። ከዚህ ኣንጻር የኢትዮዽያ መንግስት ከሌሎች ችግሩ ከደረሰባቸው መንግስታት ጋር በመተባበር  በደቡብ ኣፍሪካ ለተከሰተው ችግር ኣፋጣኝ የመፍትሔ ሃሳብ (Resolution) ለኣፍሪካ ህብረት ማቅረብ ይገባዋል። በኣፍሪካ ህብረት በኩልም የደቡብ ኣፍሪካ መንግስት ላይ በመጀመሪያ የመንጋ ጭፍጨፋውን እንዲያስቆም ከዚያም ኣደጋ ወይም ዝርፊያ የደረሰባቸውና እዚያው መቆየት የሚፈልጉት ደግሞ መልሰው የሚቋቋሙበትን ወይንም ደግሞ ካሳ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲያፈላልግ ጫና ማድረግ ይኖርበታል።
ሌላው ኣስቸኳይ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ሊቢያ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን እስላማዊ መንግስት እያለ የሚጠራው ቡድን በኢትዮዽያ የሸበርተኞች ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ ፓርላማው ኣስቸኳይ ውሳኔ ሊያደርግ ይገባዋል። ኣንድም የሰው ነፍስ ያላጠፉ ኢትዮዽያዊ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ሽብርተኛ ብሎ የሚከስ መንግስት በኣዋጅ ኢትዮዽያውያንን ኣረመኔያዊ በሆነ መልኩ የሚገድለውን ቡድን ሽብርተኛ ብሎ ኣለማወጅ ግምት ውስጥ የሚያስገባ ነው።  መንግስት ይህ ኣሸባሪ ቡድን በኣፍሪካ ህብረትም ጭምር በኣሸባሪነት እንዲፈረጅና ኣባል ኣገራትም በዚህ ኣሸባሪ ቡድን በሚጠቁበት ጊዜ በጋራ የሚመክቱበትን የኣፈጻጸም ሃሳብ በማቅረብ የመሪነት ሚና ሊጫወት ይገባዋል። በዚህም መሰረት የሊቢያ መንግስትም ይህን ኣሸባሪ ቡድን ከኣገሪቱ ጠራርጎ ማውጣት እንዲችል ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
በሶስተኛ ደረጃ መወሰድ ያለበት ወታደራዊ እርምጃ ነው። ራሱን እስላማዊ መንግስት እያለ የሚጠራው ቡድንን ከተቻለ ከሊቢያ ጠራርጎ ለማውጣት ካልሆነም ለማዳከም የሚያስችሉ ወታደራዊ እርምጃዎችን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ኣካላት ጋር በመተባበር የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ ነው። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው እንደ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኣልጄሪያ፣ ኣሜሪካ፣ ጣሊያን ና ሌሎችም ኣገራት ጋር በመቀናጀት ኣላስፈላጊ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቅራኔ ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ በማድረግ ወታደራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል። በተለይም ደካማ ከሆነው የኣገሪቱ መንግስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በማድረግና በኣገሪቱ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸውን ቦታዎች በመለየት ከግብፅና ከሱዳን ጋር በመቀናጀት ኣስቸኳይ ህይወት ኣድን ወታደራዊ ሚሽን ማካሄድ ያስፈልጋል።
መርስኤ ኪዳን
ከሜኔሶታ: ሀገረ ኣሜሪካ


1 comments: