Thursday, July 3, 2014

ብራዚላውያን የዓለም ዋንጫን ከማይደግፉበት ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹ....

 

1.ለዝግጅቱ የወጣው ገንዘብ አንገብጋቢ በሆነ መልኩ ለሌሎች ጉዳዮች መፈለጉ
በብራዚል የተዘጋጀው የዓለም ዋንጫው ልክ ሲገባደድ አገሪቷ 11 ቢሊዮን ዶላር በላይ  ወጪ ታደርጋለች፡፡
በዚህ ወጪ አገሪቷ የተሻሉ የአየር መንገዶችና የተሻሉ መሠረተ ልማቶች ቢያተርፏትም አብዛኛው ወጪ ግን የሚደረገው በእነሱ አገላለጽ ‹‹የሚባክነው›› ውድድሩ ካለቀ በኋላ ለሚረሱትና አገልግሎት ላይ ለማይውሉት ስታዲየሞች ነው፡፡ ብራዚል ለዓለም ዋንጫ ብላ የመደበችው ገንዘብ አገሪቷ ለትምህርት የምትመድበውን 60 በመቶ በጀት ያህላል፡፡ የገቢያቸውን 40.5 በመቶ የሚሆነውን ግብር የሚከፍሉት ብራዚላውያን አገሪቷ ለትምህርትና ለጤና ያላትን ቦታና ግምት እያጣች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች  የመንግሥታቸው ቀዳሚ ምርጫ ምን መሆን እንደነበረበት ግራ እንዳጋባቸው ሲኤንቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
2.ሕፃናት ለወሲብ ሥራ ከመቼውም በላይ መጋለጣቸውና መበረታታቸው 
ሕፃናትንና ሴቶችን ለወሲብ ሥራ በማሰማራት የሚተዳደሩ ግለሰቦች የዓለም ዋንጫ አገራቸው ሲመጣላቸው ገበያቸው ከመቼውም በላይ ጦፏል፡፡ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ለዚህ ቢዝነስ መጧጧፍ ታላቅ ሚና አላቸው፡፡ የሥራው ዋነኛ ደንበኞች ደግሞ ከተለያዩ የዓለም ክፍል ወደብራዚል የጎረፉት የኳስ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው አሥር ዓመት የሆኑ ወንድና ሴት ሕፃናት፣ የውጭ አገር ዜጎች በብዛት የሚንቀሳቀሱባቸው ሆቴሎች አካባቢ ባሠሪዎቻቸው አማካይነት እንዲሰማሩ ተደርገዋል፡፡ የአገልግሎት ክፍያቸውም 2.19 ዶላር ይጀምራል፡፡ እነዚህ ሕፃናት እየተንገላቱ ቢሆንም በልተው ለማደርና ረሀባቸውንም ለማስታገስ ምርጫ ስለሌላቸው ሥራውን ወደው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና መንግሥት እንደእነዚህ ዓይነት ሕፃናትን እየረዳሁ ነው ቢልም፣ የፀጥታ ኃይሎችን የጫኑ ፓትሮሎች ከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ሕፃናቱ ወደሥራቸው በግልጽ ሲሄዱ ቢያዩም ዝምታን መርጠዋል፡፡ ደንበኞችም ሕፃናቱን ከያሉበት ጥጋጥግ እየሄዱ ከመውሰድ በቅርቡ የሚታቀቡ እንደማይመስል ሚረር የዜና አውታር አስነብቧል፡፡
3.በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው በጉልበት እንዲፈናቀሉ መደረጉ
ብራዚል ካላት የሕዝብ ብዛት 16 በመቶ የሚሆኑት በድህነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለዓለም ዋንጫ መቀበያ በሚደረጉ ግንባታዎች አማካይነት 11 ሚሊዮን የሚሆኑ ብራዚላውያን ከከተማ ኑሯቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት 170 ሺሕ የሚሆኑት ዜጎች በአገሪቷ ተጨማሪ መንገዶችና ሕንፃዎች በመገንባታቸው ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ መንግሥት በርካቶችን ለዓመታት ‹‹ቤቴ›› ብለው ከሚኖሩበት ቦታ ሲያፈናቅል 1500 እስከ 22 ሺሕ ዶላር ካሳ ለተፈናቃዮች ከፍሏል፡፡ ቢሆንም ግን የቤት ዋጋ ለናረባት ብራዚል እነዚህ የካሳ ክፍያዎች በቂ እንዳልሆኑ ዋሽንግተን ፖስት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
4.የሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ መኖር አለመቻል

በብራዚል ወደ 6.6 ሚሊዮን የሚጠጋ የቤት እጥረት አለ ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ እጥረት 2500 ቤት አልባዎችን በሪዮ ዲጄኔሪዮና አሥር ሺሕ ሰዎችን ደግሞ በሳኦ ፖውሎ ጎዳናዎች ላይ እንዲኖሩ ዳርጓል፡፡ መንግሥት ለዓለም ዋንጫ ያወጣው ወጪ የተጋነነ መሆኑ ቤት አልባ ለሆኑ ዜጎቹ ስሜት አልባና ትርጉም የለሽ ሆኗል፡፡ ይባስ ብሎም በሳኦ ፖሎ የቤት ኪራይ ዋጋ ከአሥር ሺሕ የብራዚል ሪል በላይ መሆኑ ሌላው የብራዚላውያን ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ይህ የሆነው ለሚገነቡት ስታዲየሞች ከቤት ኪራይ የሚሰበሰበው ገቢ ጥሩ ይሆናል ብሎ መንግሥት በማመኑ ነው፡፡ የጉልበት ዋጋም እጅግ በጣም አናሳ ጭማሪ ተደርጎ በወር 360 ዶላር ብቻ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች በቤታቸው እንኳን መኖር እንዳይችሉ ያደረገ ሲሆን፣ ለዚህም አስተዋጽኦ ያደረገው በሳኦ ፖሎ የተገነባው ስታዲየም ነው፡፡ ይህ መሆኑ በአካባቢው የሚገኙት ገበያዎችን ዋጋ ያንራል፡፡ ይህ ደግሞ ሳይፈናቀሉ ቤታቸው የቀሩት ዜጎች ለመኖሪያ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በርካሽ ማግኘት አለመቻላቸው ጭንቅ እንደሆነባቸው  ሲኤንኤን በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡  Source  ( Reporter ) 

0 comments:

Post a Comment