Thursday, March 3, 2011

መንግስት በሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በመርከብ አስወጣለሁ አለ::

መንግሥት በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት ዝግጅቴን ጨርሻለሁ አለ፡፡ በሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ ለማስወጣት እንደ አይኦኤም (IOM)፣ ዩኤንኤችሲአር (UNHCR) እና ኦቻ (OCHA) ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በሊቢያ ኤምባሲ ካላቸው እንደ ሱዳን ከመሳሰሉ አገሮች ጋር እየሠሩ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡አምባሳደር ዲና እንዳሉት፣ በሊቢያ ካሉ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች ጋር እየተወያየን ነው፡፡ በዚያ ያሉ ዜጐቻችንም መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ያውቃሉ፡፡ በሊቢያ አሁን አውሮፕላን መጠቀም ስለማይቻል መንግሥት በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በመርከብ ለማውጣት ዝግጅቱን ጨርሷል፡፡ አምባሳር ዲና አክለውም፣ መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሊቢያ የሚገኙ ዜጐቻችንን ያስወጣል ብለዋል፡፡‹‹በቱኒዚያ ችግር እንደተከሰተ ወደ ሌሎቹ የዓረብ አገሮች ይዛመታል የሚል ግምት በመኖሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ፣ በእነዚህ አገሮች የሚገኙ የመንግሥት ተወካዮች እንዲዘጋጁ አድርገናል፤›› ያሉት አምባሳር ዲና፣ ‹‹የመንግሥት ተወካዮችም ለዜጐቻችን ምክር እንዲያስተላልፉ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ዜጐቻችን ሰላማዊ ሠልፎች በሚደረጉባቸው አካባቢዎች እንዳይገኙ መልዕክቶች አስተላልፈናል፤›› ብለዋል፡፡አምባሳደር ዲና አክለውም፣ በሊቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለመኖሩና ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው እዚያ ለመኖር ስለማይሄዱ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አይቻልም ብለዋል፡፡ባለፈው ሰኞ ኬንያ 90 ኬንያውያንና 61 የጐረቤት አገሮች ዜጐችን በአውሮፕላን በመጫን ከሊቢያ አስወጥታለች፡፡ በርካታ አገሮችም በሊቢያ ያሉ ዜጐቻቸውን በፍጥነት እያስወጡ ሲሆን፣ አሜሪካና ኔቶ በሊቢያ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ ይወስዳሉ የሚል ግምት አለ፡፡
ምንጭ (ሪፖርተር)

0 comments:

Post a Comment